Monday, April 6, 2015

Ethiopian Refugees In Yemen Appoint Actress & Human Rights Activist Yeharerwerk Gashaw As International Representative.

Ethiopian Refugees In Yemen

‹‹በአረብ ሀገራት የኢትዮጵያዊንን ችግር መወያያ እና መፍትሄ መፈለጊያ ግሩፕ›› መስራችና የየመን ስደተኞች ኮሚቴ
ግሩም ተ/ሀይማኖት::
ግልጽ መግለጫ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ
ጉዳዩ፡- የመን ያሉ ኢትዮጵያዊን ስደተኞች ችግር
በአረቡ አለም ላይ የተነሳውን አብዮት ተከትሎ የመን እስካሁን በጦርነት ስትማቅቅ ስደተኛውም ሲማቅቅ ከርሟል፡፡ከ2011 ጀምሮ ሞቅ በረድ የሚለው የእርስ በእርስ ጦርነት ስደተኛውንም ሲያሞቅ ሲያቃጥለው እዚህ ደርሷል፡፡ አሁን ተቃዋሚው የሁቲይ አማጺ ሚሊሻ ከፊል ሀገሪቱን ተቆጣጥሮ ሳለ በሳዑዲ አረቢያ አስተባባሪነት ስምንት ሀገሮች ካለፈው ሀሙስ 26/3/15 ጀምሮ የአየር ጥቃት እየሰነዘሩ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ዜጎቼን ወደ ሀገሬ አስገባለሁ ብሎ መመዝገብ ጀምሯል፡፡ ወደ ሀገር መግባት የማይችሉ የፖለቲካና የተለያየ ችግር ያለባቸው በUNHCR ስር የስደተኛነት ማረጋገጫ ወረቀት (Mandate) ይዘው ያሉት ግን በጭንቅ ውስጥ ናቸው፡፡ መጨረሻዬ ምን ይሆን? በሰው ሀገር የሚለው ጥያቄ መልስ አልባ ሆኖባቸዋል፡፡ 

ጭንቅ ውስጥ ያስገባቸው የUNHCR ቢሮ ስደተኛውን ምንም ሳያደርግለት በትኖ ቢሮውን ዘግቶ በመውጣቱ ነው፡፡ 4000 ኢትዮያዊያን እና 1000 ኤርትራዊያን ስደተኞችን ምንም አይነት ከለላ ሳይሰጥ ሰራተኞቹን ብቻ ይዞ በመውጣቱ ስደተኛው ተስፋ ቆርጦ ሞቱን መጠባበቅ እጣ ፋንታው ሆነ፡፡ አሁን በየመን ይህን መሰል ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ይግጠም እንጂ በመላው አረብ ሀገራት ኢትዮጵያዊያን በስቃይ እና ተረግጠው፣ ተገፍተው ነው የሚኖሩት፡፡ ይህ በመሆኑ ችግራቸውን የሚፈታላቸው ጥቃት ሲደርስባቸው፣ ሲጎዱ ሲታመሙ የተለያየ ችግር ሲገጥማቸው አይዟችሁ የሚል ወገንም መንግስትም የላቸውም፡፡ ለምን ይሄ ተደረገባቸው? ለምን መብታቸው ተጣሰ? የሚል ባለመኖሩ የማንም መጫወቻ በመሆናቸው በርካታ ኢትዮጵያዊያን ራሳቸው ያጠፋሉ፡፡ ታመው ወድቀው በዛው ይቀራሉ፡፡ በየሆስፒታሉ ሬሳቸው መጫወቻ እየሆነ ፍሪጅ ውስጥ ይቀራል፡፡ ታመው አስታማሚ በማጣት ችግሩ ይከፋባቸዋል፡፡ 

በፈርጅ ብዙ ችግር የታጠረው ኢትዮጵያዊ ስደተኛን ማንም ዞር ብሎ የሚያየው እኔ አለሁህ የሚለው ታጣ፡፡ በአረብ ሀገራት ያሉትን ስደተኞች ችግር በአምስት አመት በላይ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳልል ወገኖቻችን እንዲሰሙ አደረኩኝ፡፡ ለወገን ተቆርቋሪ ነን ኢትዮጵያን እንወዳታለን የሚሉትን ሁሉ ‹‹ጎበዝ ወገን ረገፈ፣ ወገን ባህር በላው፣ወገኖቻችን ኤጀንሲዎች በዘመናዊ ባርነት ሸጧቸው፣ ኤምባሲውም ረሳቸው…ያላልኩት የለም፡፡ ለካ ኢትዮጵያን እንወዳታለን የሚለው ሁላ ኢትዮጵያን አፈርና ድንጋዩን ብቻ ነው የሚወዱት ህዝቡን አይፈልጉትም እስክል ድረስ በዝምታቸው ውስጥ ሰመጡ፡፡ 

ድረ-ገጾችም (ዌብ ፔጆችም) እነሱ በሚነፍሱበት አቅጣጫ የሚያራግብ መልዕክት ካልሆነ ስለስደተኛው አጀንዳቸው አይደለምና ገጻቸው ላይ መለጠፉን አይፈቅዱም፡፡ ሰሚ ጠፋ፡፡ ያለኝ አማራጭ አንድና አንድ ሆነና ‹‹በአረብ ሀገራት የኢትዮጵያዊ ስደተኞችን መብት ጥሰት ድምጽ እናሰማ›› የሚል ላይክ ገጽ ከፈትኩ፡፡ በዛ ገጽ እና በዋናው የፌስ ቡክ ገጼ ያሰባሰብኳቸውን ልጆች በማስተባበር ‹‹በአረብ ሀገራት የኢትዮጵያዊንን ችግር መወያያ እና መፍትሄ መፈለጊያ ግሩፕ›› በዋትስአፕ አቋቋምኩኝ፡፡ በዚህ ግሩፕ ስር የበርካታ ልጆችን ችግር መፍታት ቻልን፡፡ ባለፈው ሀሙስ የመን ላይ የተጀመረውን የአየር ጥቃት ተከትሎ UNHCR ቢሮውን ጭርሱኑ ዘግቶ ሲወጣ እዚሁ ግሩፕ ላይ ተወያየንበት፡፡ ለመፍትሄ ያቀረብነው ሀሳብም የመን ካሉት ስደተኞች ውስጥ መሰባሰብ የሚችሉትን አሰባስቦ ኮሚቴ በማዋቀር ከውጭ ሊንቀሳቀሱልን የሚችሉ እንደ ከዚህ ቀደሙ አለን አለን ብለው መረጃችንን ወስደው መነገጃ የማያደርጉን ሰዎች መፈለግ እንዳለብን ወሰንን፡፡ ይህን ውሳኔ ተከትሎ እኔም በነጻ ፕሬስ ውስጥ ለሀገሬ የመናገር ነጻነት የታገልኩትን ረስተው የሚቶፍዝልኝ አጥቼ የመን መክረሜን አስመልክቼ ‹‹ግሩምዬ ያንተስ መጨረሻ ምንድን ነው?›› የሚል ርዕስ ሰጥቼ መረር ያለ መጣጥፍ ፌስቡክ ገጼ ላይ ለጠፍኩ፡፡

ወዲያው የሀረርወርቅ ጋሻው ምላሽ ሰጠችኝ፡፡ የቀድሞ ባህር ሀይሎች እና ከጅቡቲ አየር ሀይሎችን ወደ ሶስተኛ ሀገር ለማሻገር ያደረገችውን ትግል ሰምቼ ነበር፡፡ ከተወሰኑ የቀድሞ ባህር ኃይል እና አየር ሀይል ባልደረባዎች ጋር ተነጋገርኩ፡፡ ያንኑ ሀሳብ ‹‹በአረብ ሀገራት የኢትዮጵያዊንን ችግር መወያያ እና መፍትሄ መፈለጊያ የዋትስአፕ ግሩፕ ላይ እና ለተሰባሰብነው የየመን ስደተኛዎች ኮሚቴ አቀረብኩ፡፡ ከየሀረርወርቅ ጋሻው ጋር ባለን ግንኙነት ላይ ተስማማን ወከልናትም፡፡ ሌሎችም ወገኖቻችን በየመን የከፋ አደጋ እንዳያጋጥማቸው ያላችሁ በጋራ ሰርታችሁ ካለንበት ህይወትና ሞት አጣብቂኝ ውስጥ እንድንወጣ ብታደርጉ ኢትዮጵያ ከእናንተ የምትፈልገውን ፍቅር መስጠታችሁ ብቻ ሳይሆን የአእምሮም፣ የህሊናም እርካታ ይሆናችኋል፡፡
‹‹በአረብ ሀገራት የኢትዮጵያዊንን ችግር መወያያ እና መፍትሄ መፈለጊያ ግሩፕ›› መስራችና የየመን ስደተኞች ኮሚቴ
ግሩም ተ/ሀይማኖት::