ያልገባኝ እና ሊገባኝ ያልቻለ….
የመን ላለስደተኛ የደረሰው ገንዘብ የለም፡፡ በሚሳይል እና ጥይት ሞት ለተደገነበት ወገን ገንዘብ ማሰባሰብ ምን ያሳያል?
በግሩም ተ/ሀይማኖት አርብ ዕለት(05/06/15) በስዊድን ስቶክሆልም ኢትዮጵያኒዝም ቴሌቪዥን ላይ ቀጥታ ስርጭት ቃለ-መጠየቅ ነበረብኝ፡፡ በቀጥታ ስርጭቱ ላይ ከተለያየ ፓልቶክ ሩም ተሳታፊ የሆኑ ሰዎች እና ከስቱዲዮ ያሉ ጋዜጠኞች ጥያቄ ይሰነዝሩ ነበር፡፡ በፕሮፌሰር ሙሴ የሚቀርበው እዚህ ዝግጅት ላይ በየመን ስደተኛው ላይ እየደረሰ ያለውን ችግር በምችለው አቅም ባለኝ መረጃ ገለጽኩ፡፡ ስደተኛውን ኢትዮጵያዊ ወገኑ በምን መልኩ ነው መርዳት የሚችለው? የሚል ጥያቄ ከተሳታፊ ጠያቂዎች ተሰነዘረ፡፡ ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ እንደገለጽኩት የመን ያለ ስደተኛን እየአንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ሊረዳው ድምጹን ሊያሰማለት ይገባል፡፡ ገንዘብ አንፈልግም፡፡ የገንዘብ ችግርም አይደለም ወይም የምግብ ችግር አይደለም ያለብን፡፡ ህይወት የማዳን፣ ከጦርነት ቀጣና የማውጣት እርዳታ ነው የምንፈልገው አሁን እኛ ያለነው የጥይት፣ የሚሳይል እሩምታ ከሚርከፈከፍበት የሞት አውድማ ላይ ነው፡፡ ብዙዎች ወገኖቼ ሊደረስላቸው ስላልቻለ ረግፈዋል፤ ቆስለዋል፡፡ የUNHCR ቢሮ አለም አቀፍ ስታፍ ሰራተኞቹን አውጥቶ ቢሮውን ዘግቶ ምንም አይነት አገልግሎት እንደማይሰጥ ገልጾ ዘግቷል፡፡ ዝግ ቢሆንም የሶሪያ እና ኢራቅ ዜጋ የሆኑ ከ 10000 (ከአስር ሺህ) በላይ ስደተኞችን በጦርነቱ እንዳይጎዱ በሳዑዲ አረቢያ በኩል ሲያወጣ ኢትዮጵያዊያን እና ኤርትራዊያን ግን እንደዜጋው ሆናችሁ ኑሩ ብለው አሰናብተውናል፡፡..የሚል ምላሽ ሰጠሁ፡፡ በእርግጥም ሊታሰብ የሚገባው የቀለም ተጽዕኖ ካልሆነ በስተቀር ሀበሻ ነው አረብ ነው የመን ውስጥ እንደ ዜጋ መኖር የሚችለው? በ UNHCR ቢሮ ውስጥ ስደተኞችን ማበላለጥስ ተገቢ ነውን? በሌላ ጥያቄ ስለዚህ መፍትሄው ምንድን ነው? በተለያዩ ሀገራት ያሉ ኢትዮጵያዊያን በምን መልኩ ሊረዷችሁ ይችላሉ? የሚል ጥያቄ ቀረበልኝ፡፡ በተለያየ ሀገራ ያሉ ኢትዮጵያዊያኑ ወገኖቻችን ሊረዱን የሚገባው ዜጎቻችንን ከጦርነት ቀጣና አውጡልን ብለው በያሉበት ሀገር UN ቢሮ ባለበት አካባቢ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ ነው መፍትሄው :: ሶሪያ እና ኢራቃዊያኑ ከዚህ ጦርነት በኋላ መውጣታቸውን የሚገልጽ ዜና የተዘገበበት ሊንክ ለቢሮው ማቅረብ ለምትፈልጉ እና ለመጠየቅም እንዲያመቻችሁ መላክ እችላለሁ አልኩ፡፡ (በእርግጥም አሁንም ለምትፈልጉ ሊንኩ https:// እውነትም በተደጋጋሚ ውስጤ የሚጠይቀኝ ሳሰላስለው የከረምኩት ጥያቄ ነው፡፡ ወገን ጦርነት መሀል ተሳቆ በሞትና ሽረት መሀል እያለ ገንዘብ አሰባስቦ ያውም ለራሱ በቀጥታ ላይደርሰው ቢሮውን ዘግቶ ለወጣ..ለታመሙት እና ተከታታይ ህክምና ለሚወስዱት እንኳን መድሀኒት ለማያቀርብ ድርጅት መሰጠት መፍትሄ ነው? እንዲያው ለስደተኛው እንኳን በእጁ የሚደርሰው ቢሆን እንኳን እየበላህ ሙት ከተረፍክም ትረፍ ማለት ነው እላለሁ ለራሴ መልስ አልበባ ጥያቄ እያቀረብኩ ግምቴን ስሰነዝር ከርሜያለሁ፡፡ ይህን ጥያቄ በእነሱ ሳይድ በእነሱ አንግል ካላየሁት መመለስ አይደለም ማሰቡ ይከብዳል፡፡ ለነገሩ እነሱ ገንዘቡን ሰብስበዋል እየሰበሰቡም ነው እኔ ሞቱን በቅርብ እርቀት እየተጠባበኩት ነው፡፡ የእኔ እሳቤ የእኔ ቁስል እንዴት ይግባቸው? ከሌላ ጠያቂ ‹‹ገንዘብማ ተሰባስቦ የለም እንዴ እንዲያውም ወደ መን መላኩን ነው የሰማነው…? ጥያቄውን አላስጨረስኩትም፡፡ ከምር ድንግጥ ነው ያልኩት፡፡ በቃ! አጋጣሚውን ጠብቆ ገንዘብ መሰብሰብ ተግባር ላይ የተሰማራ ሀይል አለ ማለት ነው? የሚል ጥያቄ ውስጤ ተሰነቀረ፡፡ እኔ ስለምትነው ገንዘብ የማውቀው የሰማሁትም ነገር የለም፡፡ እርግጠኛ ሆኜ መናገር የምችለው የመን ያለ ስደተኛ ከየትኛውም በኩል የደረሰው ገንዘብ የለም..የሚል መልስ ሰጠሁ፡፡ በትክክሉም የደረሰ ገንዘብ የለም፡፡ አንድ ከእነሱ ጋር እገናኛለሁ የሚል የተሳሳተ መረጃ በማፍሰስ የምናውቀው ሰው ሁለት ሚሊዮን ዶላር ተሰብስቧል በማለት በስብሰባ ላይ ሲያወራ በተለምዶ ወሬው ደረጃ ሰምተን ዝም ብለናል፡፡ ለ5000 ስደተኛ ቪዛው መጥቶ ሱዳን ነው ያለው..በማለት በሮኬት ፍንዳታ የደነቆረ ጆሯችንን በቀደዳው አዝናንቶታል እግዜአብሔር ይስጠውና፡፡ ወደ ጉዳዬ ስመለስ ግን በግሎባል አሊያንስ የተሰበሰበ ገንዘብ ለኤይ. ኦ. ኤም (IOM) መሰጠቱን ጨምሮ አንድ ጠያቂ ጥያቄ አቀረበልኝ፡፡ ግርምቴ ናረ፡፡ በእርግጥም አሜሪካ ያሉ ወዳጆቼ በየቦታው ገንዘብ እየተሰበሰበ እንደሆነ ነግረውኛል በየቤተክርስቲያኑ አንድ ሰው 100 ዶላር ቲኬት እንዲገዛ መጠየቁን ሰምቻለሁ፡፡ ግሎባል አሊያንስም ቢሆን በስማችን ገንዘብ ሰብስቦ IOM መስጠት አግባብ ነው አልልም፡፡ መጀመሪያ ወገናዊነት ተሰምቷቸው ከሆነ ይህን ያደረጉት ለማን መስጠት እንዳለባቸው አለማወቃቸው ይገርማል፡፡ እዚህ የመን ውስጥ በርካታዎች በጦርነቱ መፈናቀላቸውን ኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ውስጥ ሁሉ መጠለላቸውን በየጊዜው እየገለጽኩ ነው፡፡ መድሀኒት መግዣ ያጡ አልጋ የያዙ ስንቶች አሉ? ለ IOM የሰጡት ባጀት ይዞ ስደተኛ ላይ እያላገጠ መሆኑን ሳይሰሙኝ ቀርተው ነው አልል በኢሳት ቴሌቪዥን ላይ ስንቴ ተናግሬያለሁ፡፡ ባለፈው በሳዑዲ አረቢያ ችግር ጊዜም ያደረጉት ለ IOM የሰጡት ትክክል እንዳልሆነ አሁንም ቢሆን ገንዘብ አሰባስበው ወገኖቻችን እኛን ብለው ገንዘባቸውን እንዳያወጡ የተናገርኩበት ምክንያት አለኝ፡፡ አንደኛ፡- ለስደተኛ ወገናቸው ገንዘቡ ስለማይደርስ..እነሱ እንደሚሉት እነሱ በሰጡት አይደለም IOM ኢትዮጵያዊያኑ ስደተኞችን ወደ ሀገር የመለሰው፡፡ ሁለተኛ፡- ማንኛውም ወገናችን ገንዘብ ከተጠየቀ የተጠየቀውን ገንዘብ ሰጥቶ ድምጹን ሳያሰማልን ይቀራል፡፡ ምክንያቱም ገንዘቡን ሰጥቶ እንደገና ደሞዙን አስቆርጦ ሰልፍ ወጥቶ ወገኖቻችንን አድኑልን ስለማይል ማለት ቢፈልግ እንኳን በተለያየ በኩል ወገኖቹን ብሎ እንዲጎዳ ስላልፈለግን ነው፡፡ ሊያድነን የሚችለውም ድምጹን ሲያሰማልን እንጂ ሳንቲም ስለወረወረ እንዳልሆነ እንዲያውቀው ደጋግሜ ገልጫለሁ፡፡ ሶስተኛ፡- በፍቅርም በወገናዊነትም ሲታይ በጦርነት መካከል የሚነድ ወገኑን ከዳንክ ዳን ከሞትክም ሙት ብሎ ዳቦ የሚወረውርለት ቤተሰብ እና ወገን አለ ብዬ አላምንም፡፡ ስለዚህ ከላይ በሚዘንብ ሮኬት፣ ሚሳኤል እና ጥይት ልናልቅ ነው ብለን ስንጮህ ገንዘብ ሰብስቦ መስጠት በልተህ… ማለት ነው? ከላይ ያልኩትን ሀሳብ ማጠናከር ነው፡፡ አራተኛ፡- ገንዘቡ ለስደተኛው ደረሰው እንበል ሰላም በሌለበት እንዴት ወጥቶ ሊገበያይበት ነው? ከልብ ያሰበ ከጦርነቱ መሀል ማውጣት እንጂ መንገድ ላይ ተቀምጦ ምጽዋት እንደሚጠይቅ ሰው ገንዘብ ወርወር አድርጎ ዝም ማለት ወገናዊነት አይደለም፡፡ እኛ እኮ ራበን አይደለም ያልነው አሁንም ራበን ተቸገርን አይደለም ጥያቄያችን፡፡ ጥያቄያችን በጦር መሳሪያ ልናልቅ ነው አድኑን ድምጽ አሰሙልን ነው፡፡ አምስተኛ፡- እዚህ ያለው የUNHCR ቢሮ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞችን የኢኮኖሚ ስደተኛ ናቸው እያለ ነው፡፡ ከ 100.000 በላይ ስደተኛ መመዝገቡን በራሱ መግለጫ የሚናገረው ቢሮው ከዚህ ሁሉ መዘገብኩ ካላቸው ኢትዮጵያዊያን መካከል ለ4000 ብቻ የስደተኛነት ማረጋገጫ ወረቀት የሰጠው ሌሎቹ የትኛውን ሀብት ይዘው ተገኝተው ነው ማረጋገጫው ያልተሰጣቸው? የ UNHCR ቢሮው ያልተረዳው የኢኮኖሚ ችግርም ከብልሹ የፖለቲካ ስርዓት የሚመነጭ መሆኑን ነው፡፡ ወገኖቻችንም ገንዘብ ብቻ አማራጭ አድርገው ሲያዩት የUNHCR ቢሮ ያልኩት ልክ ነው ማለት ይችላል የሚል ፍርሃት በስደተኘባው ዘንድ አለ፡፡ ለዛውም ለአይ.ኦ.ኤም ገንዘቡ መድረሱን ለማረጋገጥ ባደረኩት ሙከራ ምንም አይነት ፍንጭ እንኳን ማግኘት አልቻልኩም፡፡ በዚህ ዘመን ከጎግል የሚደበቅ የለምና ብዬ ፍለኩ (ሰርች) አደረኩ፡፡ በሳዑዲ አረቢያው ችግር ጊዜ 30.000 ዶላር ለአይ.ኦ.ኤም መሰጠቱን የተዘገበበት በርካታ ድረ-ገጽ ሲወጣ የአሁኑ ግን አንድም ሊወጣልኝ አልቻለም፡፡ መሰጠቱንም እጠራጠራለሁ ለማለት ያስደፍረኛል፡፡ ደግሜና ደጋግሜ አሁንም ማለት የምፈልገው ገንዘብ በጦርነት ቀጣና ውስጥ በጭንቅ ላለ ወገን መፍትሄ አይደለም፡፡ መቼም እነታማኝ የመፍትሄ ሀሳቡ ጠፍቷቸው፤ የችግሩ ጥልቀት ሳይገባቸው ቀርቶ ነው አልልም፡፡ ከሊቢያ ያሉትን እንዲወጡ እንቅስቃሴ መጀመራቸውን ራሱ ታማኝ ሲናገር ሰምቻለሁ፡፡ እውነት ከሆነ ለምን ለየመን ይህን አላሰበም? በጦርነት መሀል ለሚዳክር ሞቱን የሚጠባበቅን ሰው ገንዘብ ህይወቱን ያተርፍለታልን? ጥሪ ለመላው ኢትዮጵያዊያን ገንዘብ እንድታዋጡ ሳይሆን ድምጻችሁን እንድታዋጡልን ሰልፍ ወጥታችሁ UNHCR ቢሮ የሌላ ሀገር ዜጋዎችን ሲያሸሽ የእኛን ወገኖች ግን ለምን ተዋቸው በማለት እንድትጠይቁ ነው የምንፈልገው፡፡ |